News News
Minimize Maximize
« Back

“ከተሞችን አረንጓዴና ዉብ በማድረግ የከተሞችን ልማት ዘላቂነት ማረጋገጥ '''

1.የአረንጓዴነት ልማት መሠረታዊ ሀሳቦች “የአረንጓዴነት ልማት” (Green Infrastructure) ስያሜ/ቃላት መጠቀም የተጀመረው ከቅርብ ጊዜ ምናልባትም እ.አ.አ ከ2000 ዓ.ም በኋላ እንደሆነ እና በተለይ ከእንግሊዝ የሚወጡ የመንግስት ሰነዶችና እቅዶች በስፋት ይጠቀሙባቸው እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል እ.አ.አ በ2004 እና 2005 ዓ.ም የወጡት ሰስቴኔብል ኮምዩኒቲ ስትራቴጂ ፎር ታምስ ጌትዌይ እና ኖርዝአምፕተን ግሪን ኢንፍራስትራክቸር ስትራቴጂ ሰነዶች በቅደም ተከተል ይገኙበታል (Weber et al., 2006)፡፡ የአረንጓዴነት ልማት (Green Infrastructure) ሲባል አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል የሚረዳው በከተማ መሃል ወይም ዳርቻዎች አካባቢ ያለአገልግሎት የተተወ ነገር ግን በእጽዋቶች የተሸፈነና አረንጓዴ መስሎ የሚታይ ቦታ እንደሆነ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ በተቃረነ መልኩ የአረንጓዴ ቦታ ልማት ማለት ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጡ፣ ቀደም ብለው ያሉና ወደ ፊት የሚፈጠሩ፣ በገጠርም ሆነ በከተማ ሊለሙ የሚችሉ፣ ተፈጥሮአዊና ኢኮሎጂያዊ መስተጋብሮችን የሚያግዙ/የሚደግፉ፣ የማህበራዊና አካባቢያዊ ዘለቄታዊነት መርህን የሚከተል ኅብረተሰብ መገለጫዎች የሆኑ የአረንጓዴ አካላት መረብ /ኔትወርክ/ ማለት ነው (Natural England, 2008)፡፡ የከተማ አረንጓዴ ቦታዎች እቅድ ወጥቶላቸው የአንድ ኅብረተሠብን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ሊለሙ የሚችሉ፣ እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው አካባቢያዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው በአይነታቸው የተለያዩ በአረንጓዴ ተክሎች የተሸፈኑ ቦታዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል የፓርኮችና ጋርደን ቦታዎች፣ የመንገድ አካፋይ ዳርቻና አደባባይ ቦታዎች፣ የፕላዛና ክብረበዓል ቦታዎች፣ በቤቶች/ህንጻዎች/ሰፈሮች መካከል ያሉ ክፍት ቦታዎች፣ የግል /ማህበራት/ ተቋማት ግቢ፣ የእምነት ቦታዎች፣ የዘላቂ ማረፊያ ቦታዎች፣ የወንዞችና ወንዝ ዳርቻዎች፣ ሐይቆችና የሃይቆች ዳርቻዎች፣ የተፋሰስ አካባቢዎች፣ አረንጓዴ ጣሪያና ግድግዳዎች፣ ስፖርታዊ ሜዳዎች፣ የችግኝ ማፍያ ቦታዎች፣ የከተማ ግብርና፣ በከተማ መካከልና ዳርቻዎች የሚገኙ የደን ቦታዎች፣ ወዘተ. ይገኙበታል፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት የአረንጓዴነት ልማት አይነቶች ምንም እንኳ አጠቃላይ ግባቸዉ የከተሞች የአረንጓዴ ሽፋን በማሳደግ፤ የአየር ሙቀት ሁኔታ መቀነስ፣ ብዝሀ-ህይወት መጠበቅ እና የከተሞች ገፅታ ማሻሻል ሲሆን ሌሎች በርካታ ተያያዥ ጥቅሞች ያሏቸዉ በመሆኑ ጠቀሜታቸዉ የጎላና ዘለቄታዊነት ያለዉ እንዲሆን እንደየ አይነታቸው የተለያዩ የመሬት አጠቃቀም ዲዛይን፣ ስታንዳርድና የአፈጻጸም ማንዋል ተዘጋጅቶላቸዉ እንዲለሙ ይደረጋል፡፡ የከተማ አረንጓዴ ቦታዎች የተለያዩ ሕዝባዊና ግላዊ እንዲሁም የተለያየ ዋጋና አገልግሎት ያላቸው፣ በአንድ አካባቢ የሚኖር ኅብረተሰብና ተፈጥሮአዊ አካባቢ ፍላጎቶችን ያገናዘቡና ያካተቱ ፋይዳዎች ያበረክታሉ፡፡ ከነዚህም መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡ 2. የከተሞች አረንጓዴ ልማትና ዉበት ፋይዳዎች ሀ/ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ /Economic benefits/ የአረንጓዴነት ልማት ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙን በትክክል አስልቶ ማስቀመጥ ቀላል ባይሆንም በውል ሊገመት ያልቻለ ነገር ግን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሊገለጽ የሚችል ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አለው፡፡ ለምሳሌ አካባቢዎችን በአረንጓዴነት ማልማት ለአካባቢያዊና ክልላዊ ኢኮኖሚያዊ እድገት ምክንያት ሲሆኑ በተለይም ለምግብ፣ ለማገዶ፣ ለኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃነት፣ ለመድሃኒት እንዲሁም ለሥራ ፈጠራ እና ለአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በዘርፉ የተደረጉ የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ለ/ ማህበራዊ ፋይዳ /Social benefits/ በማህበራዊ ጥቅም ረገድ ተደራሽና ጥራቱ የተጠበቀ አረንጓዴ ቦታ ከፍተኛና ዕምቅ የሆነ ጥቅም እንዳለው የሚታወቅ ሲሆን እነዚህንም በሦስት ከፍሎ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ የጤና መሻሻል እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተግባሮች መጨመር፣ የስነ ልቦና እና የአእምሮ ደህንነት ማጎልበት እና ማህበረሰባዊ ግንኙነትን እንዲሁም አብሮነትን ማጠናከር ናቸው፡፡ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት የአረንጓÁ ቦታዎች አቅርቦትና አገልግሎት በጨመረ ቁጥር ሰዎች ለስፖርታዊ ጨዋታዎችና እንቅስቃሴዎች ያላቸው ፍላጎት እንደሚጨምር ታውቋል፡፡ በተጨማሪም አረንጓዴ ቦታዎች ማህበራዊ መስተጋብርን በማሻሻል የዜጎች አብሮነትን ያጠናክራሉ፡፡ ይህም የማንኛውም መንግስት ፍላጎትና ቅድሚያ ከሚሰጣቸው እሴቶች አንዱ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ሐ. አካባቢያዊ ፋይዳ /Environmental benefits/ የከተማ አረንጓዴነት ልማት ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በተጨማሪ በርካታ ከአካባቢ ጋር የተያያዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ ከእነዚህም መካከል የአየር ብክለት ምንጭ የሆኑትን፣ የድምጽ ብክለትን፣ የከተማ ጎርፍን እንዲሁም በበጋ ወቅት የሚኖረውን ከፍተኛ የከተማ ሙቀት ተጽዕኖን፣ የንፋስ ፍጥነትን በመከላከል በንፋስ የሚመጣ አደጋን መቀነስ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ የከተማ አረንጓዴነት ልማት በካይና የአካባቢን ሙቀት የሚጨምሩ እንደ አሞኒያ (NH3)፣ ካርቦንዳይኦክሳይድ (CO2)፣ ናይትሮጂን ኦክሳይዶችን (NO)፣ ሌሎች ንጥረ ነገሮች እና ሰልፈርዳይኦክሳይድ (SO2) የመሳሰሉትን ከአየር ውስጥ በመምጠጥ የከተሞች አየር ጥራትን ለማሻሻልና የአየር ንብረት ለውጥ ክስተቶችን ለመቀነስ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ ለምሳሌ፡- በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ አንድ ጤናማ ያላረጀ ዛፍ 13 ፓውንድ /5.89 ኪ.ግ/ የሚሆን ካርቦን በአመት የሚያጠራቅም ሲሆን በአንድ ኤከር መሬት /0.4 ሄ/ር/ ያለ ደን 2.6 ቶን ካርቦን በማጠራቀም በከባቢ አየር ውስጥ ያለውን የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን ሊቀንስ ይችላል፡፡ እነዚህ ጥቅሞች በተናጠል የሚገኙ ሳይሆኑ በዲዛይን የታገዙና በእንክብካቤ የተያዙ የአረንጓዴነት ልማት ውጤቶች ናቸው፡፡ በተመሳሳይም በበጋ ወቅት የሚኖረውን ከፍተኛ የከተማ ሙቀት ለማሻሻል ይረዳሉ፡፡ መ. ለውኃ ዑደት የሚሰጠው ፋይዳ /Hydrological benefits/ በተፈጥሮ አካባቢያዊ ላይ የሚፈጠር ለውጥ በውኃ ተፈጥሮአዊ ኡደት እና ይዘትን የማዛባትና የመቀየር አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡ ከተሞች ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ መልኩ የመሬት ንጣፋቸው አብዛኛውን ጊዜ ውኃ በማያሰርግ አስፋልትና አርማታ ውጤቶች የተገነቡ በመሆናቸው በአካባቢያዊ የውኃ ሃብት እና ስነምህዳራዊ ክስተቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አላቸው፡፡ የአረንጓዴ ልማት በዚህ ረገድ ሁለት ዋና ዋና ጥቅሞች ይሰጣል፡፡ እነዚህም የጎርፍ ክስተት መቀነስ እና የውኃ ጥራት መጠበቅና ማሻሻል ናቸው፡፡ በከተማ እና ከተማ ዳርቻ ያሉ ዛፎችና እጽዋቶች በተፋሰስ አካባቢዎች የሚገኙ የጎርፍ ውኃን መጠን በመቀነስና በማዘግየት፣ የዝናብ ውኃ ወደ አፈርና መሬት ውስጥ ስርገትን በማፋጠን ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣሉ፡፡ በሌላ በኩል የጎርፍ ውኃ በካይ አካላትን በመሸከምና ከውኃ አካላት ጋር በመቀላቀል ለብክለት አስተዋጽኦ ማድረጉ የሚታወቅ ሲሆን የአረንጓዴ ቦታዎች ልማትን ማስፋፋት ግን ይህን ችግር በመቅረፍና የውኃ ጥራትን በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡ ሠ. ኢኮሎጂያዊ ፋይዳ /Ecological benefits/ የከተማ አረንጓዴ ቦታዎች የተለያዩ እጽዋትና እንስሳት መኖሪያና ማረፊያ ቦታዎች በመሆን የሚያገለግሉ ሲሆን ውጤታማ እና በፕላን የታገዘ የከተማ አረንጓዴ ቦታዎች የተለያዩ ዝርያዎች እንዲንቀሳቀሱ፣ እንዲሰራጩና እንዲባዙ ምክንያት በመሆን ያገለግላሉ፡፡ ቀደም ብሎ ለተለያዩ አገልግሎት የዋሉና በኋላ ግን በተለያየ ምክንያት የተተው የከተማ መሬቶችን ከደረሰባቸው ጉዳት አገግመው ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ጥቅም እንዲውሉ ለማድረግ የአረንጓዴነት ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም የተተው እና የተጎዱ የከተማ ቦታዎችን እንዲያገግሙ ማድረግ በአገልግሎት ላይ ካሉ አረንጓዴ ቦታዎች ጋር ያለውን ኔትወርክ በመፍጠር አገልግሎቱን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ያሸጋግረዋል፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ የከተማን ብዘሃ ህይወት ለመጠበቅና ከከተማ ውጪ ካሉት የጥብቅ ቦታዎች ጋር ለማስተሳሰር፤ ተፈጥሮኣዊ የውሃ፣ የከባቢ አየር (athmosphere)፣ የፀሐይ ብርሃንና የአፈር ትስስር በመፍጠርና በማቀናጀት የከተማን ስነ ምህዳር ይጠብቃሉ፡፡ ይሁን እንጂ በሀገራችን ከተሞች ለአረንጓዴነት ልማት የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከላይ የተዘረዘሩት ፋይዳዎች በሚፈለገው ደረጃ እየተገኙ አይደለም፡፡ ማህበራዊ ፋይዳዉን ለአብነት ሲታይ የአረንጓዴ ቦታዎች አቅርቦትና አገልግሎት በጨመረ ቁጥር ሰዎች ለስፖርታዊ ጨዋታዎችና እንቅስቃሴዎች ያላቸው ፍላጎት እንደሚጨምር፣ አረንጓዴ ቦታዎች ማህበራዊ መስተጋብርን በማሻሻል የዜጎች አብሮነትን እንደሚያጠናክር ይህም የማንኛውም መንግስት ፍላጎትና ቅድሚያ ከሚሰጣቸው እሴቶች አንዱ እንደሆነ ጥናቶች የሚያመላክቱ ቢሆንም በሀገራችን ከተሞች ግን ይህ ሁኔታ ተግባራዊ እየሆነ አይደለም፡፡ ለዚህም ዋነኛ ምክንያቶች ከአረንጓዴነት ልማት ዓይነቶች አንጻር በሚለው ርዕስ ስር በዝርዝር ተገልጸዋል፡፡ 3. ለአየር ንብረት ለዉጥ የማይበገር የከተሞች አረንጓዴ ልማትና ዉበት ዓላማዎች 1. የስትራቴጂው አላማዎች • የከተሞች አረንጓዴነት ልማት ላይ ህብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ ቀጣይነት ባለውና ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ማድረግ፤ • አረንጓዴ ቦታዎቻቸው በፕላን መሠረት እንዲለሙ ማድረግ፤ • የአረንጓዴነት ልማት አገልግሎት አሰጣጥ፣ ዘርፈ ብዙ፣ ጥራት ያለው ፍትሀዊና ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ፣ • ዘላቂ ማረፊያዎች ወደ መታሰቢያ ፓርክነት እንዲቀየሩ ማድረግ፤ • ነባር የቀብር ስፍራዎች ለመልሶ መጠቀም (Recycling) አገልግሎት እንዲውሉ ማድረግ፣ • የአካባቢ ተፈጥሮ ሚዛንና ብዝሃ ህይወት እንዲጠበቅ ማድረግና የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም፣ • የአረንጓዴ ልማት ዓይነቶችን (Components) ያገናዘበ አሰራር በመዘርጋት ከተሞችን ለኑሮ ምቹ ማድረግና ኢኮ-ቱሪዝምን ማስፋፋት፣ • ከተሞቻችን ከብክለት እንዲፀዱና በእጽዋት እንዲዋቡ ማድረግ፣ • በዘርፉ ያለውን የማስፈጸም አቅም በመገንባት የከተሞች አረንጓዴነት ልማት በዘመናዊ አሰራር የታገዘ እንዲሆን ማድረግና 4. የከተሞች አረንጓዴ መሰረተ ልማት ስታንዳርድ ምንነት • የከተሞች ፕላን ሲዘጋጅ በከተማ ፕላን ዝግጅትና ትግበራ ስትራተጂ በተቀመጠው መሰረት 30 % መሬት ለመንገድና ለመሰረተ ልማት፣30 % ለአረንጓዴ ቦታዎችና ለጋራ መጠቀሚያዎች እና 40 % ለህንጻ ግንባታ እንዲውል መደረግ አለበት፤ • የክልል እና የከተማ ፕላን ሲዘጋጅ የአረንጓዴ መሰረተ ልማትን በማካተት መሆን ይኖርበታል፤ ለምሳሌ የአዲስ መንገድ ዝርጋታ ወይም ሌሎች ፕሮጀክቶች ሲኖሩ በቂ የአረንጓዴ ቦታ ሊተው ይገባል፤ • የከተሞች አረንጓዴ መሰረተ ልማት ከዘላቂ አካባቢያዊ ስራዎች ጋር መጣጣም ይኖርበታል፡፡ • የከተሞች አረንጓዴ መሰረተ ልማት በአካባቢው ህብረተሰብ ፍላጎት መተዳደር ይኖርባቸዋል፡፡ • ለአረንጓዴ ቦታዎች ልማት በሁሉም ደረጃ እና በመንግስት ሴክተሮች በቅንጅት መተግበር ይገባዋል፡፡ • በየደረጃው የዘርፉን ስራ የሚያስፈፅመው አካል የግለሰቦችን በማበረታታት እና የውድድር መንፈስ በመፍጠር በአረንጓዴ ልማቱ በማሳተፍ በከተሞች የሚኖረውን የአረንጓዴ ሽፋን ማሳደግ ይኖርበታል፡፡.