News News
Minimize Maximize
« Back

የከተሞች ፎረም በጥንታዊቷ ጎንደር “የከተሞች ዘላቂ ልማትና መልካም አስተዳደር ለህዳሴያችን!!”

የከተሞች ፎረም በጥንታዊቷ ጎንደር "የከተሞች ዘላቂ ልማትና መልካም አስተዳደር ለህዳሴያችን!!" አለም በድቅድቅ ጨለማ በተዋጠበት፣ በስልጣኔ እጦት እጅና እግሩን በተያዘበት፣ እንዲህ እንደዛሬው ባልዘመነበት እና አይኑን ባልገለጠበት በዚያ ጥንት ዘመን የሀገራችን ሊቃውንት የቀን መቁጠሪያ አቡሻክር፣ የባህል መድሀኒት ዝርዝሮችን የያዙ በርካታ መፃህፍት፣ የተለያዩ ጥንታዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶችን ለአለም በማበርከት፣ ዘመናዊ አስተዳደርን ከአለም ቀድማ ለመጀመሪያ ጊዜ የዘረጋች አገር ኢትዮጵያ እንደነበረች የተረጋገጠ እውነት ሲሆን፤ ለዚሀ ደግሞ ቀዳሚ ተጠቃሿ፤ የአንድ ወቅት የአገራችን መናገሻ የነበረችው ጎንደር እንደሆነች ታሪክ በሰፊው ያስረዳል፡፡ በሰሜን ምእራብ ኢትዮጵያ የምትገኘው፣ እ.ኤ.አ በ1635 በአጼ ፋሲለደስ (በ1624 አ/ም የነገሱ) የተቆረቆረችው ጎንደር ከተማ የበርካታ (ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ) እሴቶች መገኛ ምንጭ ነች፡፡ በሀገሪቱ የታሪክ እምብርትነቷ፣ በቀዳሚና ዘመናዊ አስተዳደር ዘይቤዋ፣ በቱባ ባህሏ፣ የተለያዩ ሀይማኖቶች (በተለይ የእስልምናና የክርስትና) እምነት ተከታዮች ተስማምተው በፍቅር የሚኖሩባት ምድርነቷ፣ የ44 ቤተ-ክርስቲያናትና አድባራት መገኛ መሆኗ፣ በዩኔስኮ በአለም ቅርስነት የተመዘገቡ የውብ ኪነ-ህንፃዎችና የአብያተ-መንግስታት ግብረ-ህንፃዎች (ተዝወትረው ከሚጎበኙት ሀይማኖታዊና ታሪካዊ መስህቦች መካከል የአፃ ፋሲለደስ ቤተ-መንግስት የመዋኛ ስፍራ፣ የደብረ-ብርሀን ስላሴ ገዳምና የቁስቋም ቤተ-ክርስቲያን ዋና ዋናዎቹ ናቸው) መገኛነቷ፣ በአፄ ዮሀንስ በተገነባው ቤተ-መፃህፍቷ፣ በጥንታዊ የንግድ ተቋማት ማእከልነቷ፣ በቱሪዝም መስህብነቷ፣ ከሁሉም በላይ የጀግኖች መፍለቂያነቷ . . . ከሁሉም መሰል የአገራችን አካባቢዎች ጎንደርን ("ጎንደር" የክፍለ-ሀገሩም የከተማውም ስያሜ ሲሆን ይህ አይነቱን አሳያየም (በ"Archetype" ላይ የተሰሩ ጥናቶች ሲፈቱት "image, ideal, or pattern that has come to be considered a universal model. Archetypes are found in mythology, literature, and the arts, and are important aspects of both philosophical and psychological thought." ይሉታል) በራሱ ያመራምራል ብቻ ሳይሆን ያወያያል፤ ያነጋግራልም) ስሟ ጎላ፤ ከፍ ብሎ እንዲኒኝ አድርጎታል። እጅጉን ሲበዛ ዜማ የተንቆረቆረላት፣ የተተረከላት፣ የተፃፈና የተደረሰላት፣ ቅኔ የተዘረፈላት ጎንደር፣ የመክብር ስሟን ያገኘችው - ‹‹አንተም በዚህ ጎን እደር፤ አንተም በዛ ጎን እደር›› ከሚል የመቻቻል፣ መተሳሰብ፣ ፍትሀዊነት፣ አስተዋይነት ወዘተ መሰረታዊና የሰለጠኑ (በተለይ ባሁኑ ዘመን ሲመዘን) አስተሳሰቦች መሆኑ ይነገራል፤ ያሳምናልም። (ይህን ስንል ግን "እቅጩ" ላይ የመድረሱን ጉዳይ ለስነቃል/Folklore ተመራማሪዎች በመተው ነው)፡፡ በሰሜን ምእራብ ኢትዮጵያ፤ ከአዲስ አበባ 720፣ መቀመጫውን ባህርዳር ካደረገው የክልሉ ዋና ከተማ/ባህር ዳር 178 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ጎንደር ከተማ 5ሺ 560 ሄክታር የቆዳ ስፋት፣ ከባህር ጠለል በላይ 2ሺ 200 ሜትር ከፍታ አላት። 

የህዝብ ብዛቷ 303ሺ 81 የሆነው ጎንደር ከተማ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ እና ጎብኚዎች ከሚያዘወትሯቸው በርካታ የኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ በቀዳሚነት ተጠቃሽ ነች፡፡ በአብዛኛው ቱሪስቶች ለጥምቀት በዓል በአጼ ፋሲል መዋኛ ስፍራ በመገኘት ልዩ የሆነውን የአከባበር ስርዓት ይታደማሉ፡፡ እግረ መንገዳቸውንም በከተማዋ የሚገኙ በርካታ ቅርሶችንና ታሪካዊ ቦታዎችን እየተዘዋወሩ መጎብኘት የሁል ጊዜ ተግባራቸው ነው። ይህም የጎንደር የቱሪዝም መስህብ/ሀብት መሆን፤ መንግስት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አማካይነት - "ኢትዮጵያን እስከ 2012 አ/ም ባህላዊ ሀብቶቿና የተፈጥሮ መስህቦቿ ለምተው በቱሪዝም መዳረሻነት ከመጀመሪያዎቹ 5 የአፍሪካ አገራት አንዷ እንድትሆን ማድረግ" በማለት የሰነቀውን ተልእኮ፤ ወይም (Strategic) ራእይ በሚገባ እውን ከሚያደርጉት የአገራችን የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች መካከል አንዱ ያደርገዋል፡፡ በ1628 ዓ.ም በአፄ ፋሲለደስ የተቆረቆረችው እና ከ250 አመታት በላይ በኢትዮጵያ ማእከላዊነት (የኢትዮጵያ መንግስታት መቀመጫና የሀገሪቱ ዋና ከተማ) ያገለገለችው ጎንደር ከተማ ዘመናትን ካስቆጠሩ 23 የአለማችን ጥንታዊ ከተሞች አንዷ መሆኗን በቅርቡ የአለም የዜና አውታሮች ተቀባብለው ዘግበዋል፡፡ ከ23ቱ ጥንታዊ ከተሞች ተርታ የተሰለፈችው ጎንደር በ21ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧም ተገልፇል። አገራቱም 4 ከአፍሪካ፣12 ከኤዥያ፣ 4ቱ ከአውሮፓ፣ 2 ከሰሜን አሜሪካ እና አንዱ ከደቡብ አሜሪካ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ለመንደረድሪያ ያህልና ለጎንደር እንግዶች ግንዛቤ ይሆን ዘንድ ስለጎንደር ከተማ ይህን ያህል ካልን ወደተነሳንበትና አጀንዳችን ወደሆነው "የከተሞች ፎረም" አስተናጋጅነቷ እንለፍ። የታሪክ እምብርት የሆነችውና በአለም በጥንታዊ ከተማነት ማእረግ ላይ የተቀመጠችው ጎንደር ከተማ በቅርቡ ሰባተኛውንና "የከተሞች ዘላቂ ልማትና መልካም አስተዳደር ለህዳሴያችን!!" በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን "የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም" ለማስተናገድ ቅድመ ዝግጅቷን በማጠናቀቅ ላይ ትገኛለች፡፡ ከሚያዝያ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በሚቆየው በዚህ መድረክ 200 ከተሞች፣ የእነዚሁ ከተሞች እህት የሆኑ ሌሎች የውጭ አገር ከተሞች፣ እንዲሁም 20 ኩባንያዎች (በስድስተኛው የከተሞች ፎረም 166 ከተሞችና 17 ኩባንያዎች ተሳታፊ ነበሩ) ተሳታፊ የሚሆኑ ሲሆን፤ ይህም ጎንደርን ከፍተኛ ዝግጅትና መስተንግዶ ይጥይቃታል። ሰሞኑን ከስራ ሀላፊዎቹ እንደተሰማው ከሆነ በዝግጅት በኩል ጎንደርን የሙያሳስባት ምንም ነገር እንደሌለ ነው። የበአሉ አዘጋጆች እንደሚሉት ጎንደር "ምን ጠፍቶ፤ ሁሉ በጄ ሁሉ በደጄ፤ እናንተ ብቻ ኑልኝ እንጂ ሁሉም ነገር ምሉእ በኩለሄ ነው" እያለች ነው። ለዚህም የአማራ ክልል መንግሥት ለፕሮግራሙ ከመደበው 25 ሚሊዮን ብር በተጨማሪ፣ የጎንደር ከተማ አስተዳደርም ተጨማሪ በጀት በመመደብ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያካሄደ መሆኑን፤ ጎንደርም ለዝግጅቱ ድምቀትና ለእንግዶቿ መስተእንግዶዋን የተዋጣለት ለማደረገ ሳትታክት በመስራት ላይ መሆኗ ሁሉ ሳይቀር ተሰምቷል። የከተሞች ሳምንትን ያደምቅ ዘንድ ቀደም ሲል ፈርሶ የነበረውና ዝነኛው የፋሲለደስ ባህላዊ የኪነት ቡድን እንደገና መቋቋሙም የዚሁ የጎንደር "የከተሞች ፎረም" ዝግጅት አካል መሆኑም ተነግሯል። የፀጥታው ጉዳይም ምንም የሚያሳስብ ነገር እንደሌለ፤ ፍፁም ሰላማዊ መሆኑና ባለፈው ተከስቶ የነበረው ግርግርና ሁከት ሁሉ መክሰሙን የበአሉ አዘጋጅና ተባባሪዎች መግለፃቸውም የበአሉን ድምቀትና ሰላማዊ ሁኔታ ከወዲሁ የሚያመላክት ነው። የእስከዛሬዎቹ "የከተማ ቀን" በአላት ምን ገፅታ ነበራቸው? የሚለውን እናንሳና ትንሽ ወደኋላ መለስ በማለት የስድስቱን አመት በአል አከባበር ሁኔታ ባጭሩ እንቃኝ። በ2002 የክብረ-በአል ጥንስሱን አዲስ አበባ ያደረገው "የከተሞች ቀን" 46 ከተሞችን ብቻ አሳታፎ ነበር በአሉን ያከበረው፡፡ በወቅቱም አዲስ እንደዋና ከተማነቷ "ወይ ሸገር ወይ ሸገር፤ ወይ አራዳ ሆይ . . ." በማለት ነበር ታዳሚዎችዋን ተቀብላ ያስተናገደችው። በአሉን በድል ካጠናቀቀች በኋላም ቀጣዩን ችቦ ትለኩስ ዘንድ እድሉን ለባለተራዋ፤ ለደቡቧ ዋና ከተማ ሀዋሳ አሰረከበች፡፡ ሀዋሳም ከአስፈላጊውና ማራኪ ዝግጅት በኋላ "ዳዬ ቡሾ . . ." በማለት የተቀበለቻቸውን እንግዶቿን አንቀባራ አስተናገደች፡፡ በአሉ ቀጥሏል፤ ቀጥሎም ፊቱን ወደ መቐለ አዙሯል። ማንነቴን ማሳየት አለብኝ በማለት ይመስላል፤ መቐለ ከተማም እንግዶቿን "አዝልቃ እንኳዕ ደሓን መፃእኹም!" በማለት በልዩ አቀባበል አስተናገደች። በዚህ ጊዜ ነበር "የከተሞች ቀን" የሚለው ስያሜ ለበአሉ በቂ እንዳልሆነ ታምኖበት "የከተሞች ሳምንት" የሚለውን የዳቦ ስም በ2004 ዓ.ም ያገኘው። ከዚህ ሁሉ በኋላም መቐሌም ለባለተራዋ ከተማ አስተላልፋ ዝግጅቷን አጠናቀቀች። አደራውን ከመቐለ የተቀበለችው የስምጥ ሸለቆዋ፤ የጨፌ ኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ አዳማ ‹‹በጋ ነጋን ዱፍተን›› በማለት አዲሱን ስያሜ ከአዲስ መሪ ቃል ጋር አጣምራ በዓሉን አክብራ ለባለተራዋ ባህር ዳር አስረከበች። ውቢቷ ባህርዳርም ለከተማማ እኔን የሚስተካከል የለም በሚል ወኔ ይመስላል፤ አርሂቡ በማለት ራስዋን ለዝግጅቱ ድምቀት ኳኩላ በሯን ክፍት በማድረግ እንግዶቿን ተቀበለች፤ ይህ ቀረሽ በማይባል ደረጃም አስተናገደች። ቀጥሎ ወዴት፤ ማነሽ ባለተራ? ከእስከ ዛሬዎቹ አዘጋጆች ልምድ የቀሰመችው የፍቅር ከተማዋ ድሬ አብሽር መርሀባ ብላ እራሷን በአይቮሪ ቀለም አሸብርቃ በ2007 ዓ.ም ሳምንቱን በድምቀት አከበረች። በወቅቱም "የከተሞች ሳምንት"ን በአል በተመለከተ ከሌሎች ሀገራት ልምድ በመውሰድ ወደ ፎረምነት እንዲቀየር፤ በየአመቱ ይከበር የነበረውም በየሁለት አመቱ እንዲሆን በክልሎች ድሬ ላይ የጋራ ውል ታሰረ፡፡ ሰባተኛውንና የዘንድሮውን "የከተሞች ፎረም" በአል ለማክበር ተራውን ከድሬ ዳዋ በመውሰድ የዝግጅት ጊዜውን በጉጉት ስትብቀው የነበረችው ጎንደር ድንቅ ትውፊቷንና ቱባ ባህሏን ልታሳየን፤ የ382 አመት የከተማነት ሚስጥሯን ልታስዳስሰን፤ የእንግዶቿን ልብ ልታርስና ከእስከዛሬዎቹ ልቃ ለመታየት በዓሉንና እንግዶቿን በጉጉት፣ ተፎካካሪነቷን ደግሞ በተግባር ለማስመስከር ወገቧን ታጥቃ ደፋ ቀና ማለቷን ተያይዛዋለች፡፡ የከተሞች ፎረም የሚከበርበት ዋና አላማ ከተሞችን ማስተዋወቅ፣ እድገታቸውን መደገፍ እና በዕርስ በዕርስ የፉክክር መንፈስ እንዲያድጉ ለማድረግ ሲሆን፤ በፎረሙ ተሳታፊ የሚሆኑ ከተሞች በእስከዛሬው ሂደታቸው ያስመዘገቧቸውን መልካም ሥራዎች ይዘው የሚቀርቡበት፤ ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበትና ለከተማ ነዋሪዎች መረጃ የሚሰጡበት፤ መድረክ ከመሆኑም በላይ እርስ በርስ የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት መድረክ እንደሚሆን ይጠበቃል። ይህ ብቻም አይደለም፤ የኢትዮጵያ ከተሞች የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲዳብር የኢንቨስትመንት፣ የገበያና የቱሪዝም ትስስራቸው የጠበቀ እንዲሆን ማድረጉም ሌላው የፎረሙ ፋይዳ ነው። የከተሞች ፎረም በሚካሄደባቸው ከተሞች ለበዓሉ ድምቀት ጭምር በማሰብ የሚሰሩ የመሰረተ ልማት ስራዎች አሉ፤ እንደ ዋና መንገድ እና የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የመንገድ መብራት፣ የከተማ እድሳት፣ የስቴዲየሞች እድሳት ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉ ስራዎች ይሰራሉ፡፡ እነዚህ ተግባራት ግን የይድረስ ይድረስ እየሆኑ ጉዳቶችን እያደረሱ ይገኛሉ። ይህ ችግር በከተሞች ፎረም በዓል ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም በአላት ላይ እታየ ያለና አፋጣኝ መፍትሄን የሚያሻ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የብሄር ብሄረሰቦችን በዓል ለማክበር የአስፓልት ንጣፍ መንገድ ተሰርቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ከተሰራ ስድስት ወር ሳይሞላው መንገዱ ውሀ እያቆረና ጭቃ እየሆነ ለመኪኖችና ለህብረተሰቡ ችግር ሆኖ ታይቷል። ይህንን አነሳን እንጂ ክብረ በዓሎች የሚከበሩባቸው ሌሎች የክልል ከተሞች በዓሉ ሲደርስ የሚደረግላቸው ዝግጅት በዓሉ ሲልፍ ቀጣይነቱን ያጣል፤ ለመንገድ የሚሰሩ መብራቶች ሁነቱ ሲያልፍ መብራት እንደማይሰራ/እንደማይበራ ይነገራል፡፡ ይህ በዋናነት በዓልን ከማክበር ያለፈ ራዕይ ወይም አላማ ይዞ ያለመነሳት ችግር ነው፡፡ ችግሩ ግን በቀጣይም ችግር ሆኖ እንዳይቀጥል በበዓላት ያለን ተሳትፎና ፍቅር፣ የከተማችን ጽዳት፣ እንግዳ የመቀበል ፍላጎት ሁሉ ከበዓላት ውጪም ቢቀጥል መልካም ነው፡፡ የራሳችንን ከተማ ውበት ጽዳት በመጠበቅ ታሪካዊ እና ትውፊታዊ የሆኑ ባህሎችን በመጠበቅ ከተማችንን ሳቢና ዘመናዊ ባህላችንን ጥንታዊነቱን ጠብቀን ማቆየት አለብን፤ መንግስትም ዘላቂነታቸው ላይ መስራት ይጠበቅበታል የሚለው ተጨማሪ መልዕክቴ ነው ሰላም፡፡ አዘጋጁ፡- ጸሐፊዋን በኢሜይል አድራሻቸዋ (zqueenofmom@gmail.com) ማግኘት ይቻላል።