News News
Minimize Maximize
« Back

በህብረተሰብ ተሳትፎ የታገዘ የዕድገት ግስጋሴ ላይ ያለች ከተማ - ፍቼ

የፍቼ ከተማ በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን ስር ከሚገኙ ከተሞች አንዷ ስትሆን ከአዲስ አበባ ከተማ በስተ-ሰሜን በ112 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች ፡፡ ከተማዋ 4 ቀበሌዎች ያሉዋት ሲሆን ደረጃዋም በ2ኛ "B ትመደባለች፡፡ በፍቼ ከተማ ከ65,000 ባላይ ህዝብ ይኖራል፡፡ ከተማዋ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች የሚኖሩባት ሲሆን የተለያዩ ሃይማኖቶች ማለትም ኦርቶዶክስ፣ ፕሮቴስታንት፣ ሙስሊም እና ሌሎች የ ሃይማኖት ተከታዮች በመቻቻልና በመከባበር የሚኖሩባት ከተማ ናት፡፡ የፍቼ ከተማ ከተቆረቆረች ከ 174 አመታት በላይ ቢሆናትም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር ጥያቄዎች መመለስ ባለመቻሉ ወደ እድገት ጎዳና ሳትገባ መቆየቷ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ የከተማውን ችግር ለመፍታት በነበረው ሂደት ትኩረት የተሰጠው በችግሩ የተጎዱ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸዉ፣ አቅመ ደካሞች፣ ወጣቶችና ሴቶችን ወዘተ የህብረተሰብ ክፍሎችን መለየት ዋነኛው ሲሆን በማስከተልም ችግሮቹን ለመፍታት ቁልፍ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በዚህም ከተማዋ የሚፈለገውን የልማትና መልካም አስተዳዳር ስራዎች ማከናወን እንድትችል የፍቼ እድገት ከየት ወዴት? በሚል ርዕስ ከፍተኛ ግምገማ በማድረግ አመራሩ ጋር የነበሩ ተግዳሮቶችን፣ ህብረተሰቡ ጋር የነበሩ ተግዳሮቶችን እንዲሁም ሰራተኛው ጋር የነበሩ ችግሮችን በመለየት ሰፊ ውይይት እና ኮንፈረንስ በተለያዩ መድረኮች ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተካሂዶ ነበር፡፡ በከተማዋ በተለዩ ችግሮች ዙሪያ እንዲወያዩ የተለዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም የከተማው ነዋሪ ህዝብ፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ የድርጅት አባላት፣ በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ማህበራት፣ ነጋዴዎችና ባለሀብቶች፣ በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ የከተማዋ ተወላጆች፣ ተማሪዎችና መምህራን፣ ሴቶች፤ ወጣቶች የእምነት አባቶች እና ሌሎች ተሳታፊ ነበሩ፡፡ የከተማዋን ነዋሪ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስና ታሪኳን ለመቀየር መንግስት ያወጣቸውን የከተማ ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ መሠረት በማድረግ አመራሩና ህብረተሰቡ በቅንጅት ባካሄደው የጋራ ርብርብ ከተማዋ ወደ ልማት ህዳሴ መስመር ከገባች አምስት አመታትን አስቆጥራለች፡፡ ካለፉት አምስት አመታት ወዲህ አመራሩ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን የህዝብ ተሳትፎና ንቅናቄን እና የልማት አደረጃጀቶችን በመፍጠር በመልካም ተሞክሮነት የሚጠቀሱ የልማት ስራዎች በከተማዋ ተከናውነዋል አሁንም በመከናወንም ላይ ይገኛሉ፡፡

በከተማዋ የልማት ኃይሎችን አደራጅቶና አቀናጅቶ በመምራት፣ አሳታፊ እቅድ በማዘጋጀትና ህዝባዊ መሠረት ያላቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን በመመለስ ረገድ ባለፉት ጊዜያት አበረታች ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ለዚህም በማሳያነት የፍቼ ከተማ አስተዳደር በከተማው ለረዥም ጊዜ ስር ሰዶ የቆየውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን የህብረተሰቡን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ባማከለ መልኩ በመፈጸም ረገድ አመርቂ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ የፍቼ ከተማ አስተዳደር በሚወያጣቸው ዕእቅዶች ህዝቡ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት በማድረግ በተለይም የነዋሪውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቹን በሚፈፈቱ የመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ሕብረተሰቡ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በጉልበት፤ በገንዘብ እና በቁሳቁስ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በከተማው የታቀዱ ስራዎችን ከግብ ለማድረስ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፤ የቀበሌ መዋቅሮች እና በየደረጃዉ ያሉ የልማት ሠራዊቶችን ለተፈለገ አላማ ለማዋል እየተሰጠ ያለዉ አመራር እያደገና እየተሻሻለ በመምጣቱ የከተማዉ ልማት ከጊዜ ወደ ጊዜ በፈጣን ሁኔታ እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ በህብረተሰብ ተሳትፎና ንቅናቄ ያስመዘገበውን ውጤት በመልካም ተሞክሮነት በመቀመር ለሀገራችን ከተሞች በማስፋት ሌሎች ከተሞች የከተማዋን ተሞክሮ እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል፡፡ በከተማው የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ የተሰራው ስራ መንግስት የነደፈውን የልማትና የድህነት ቅነሳ ፖሊሲ ከመተግበር አኳያ ለሥራ ፈላጊ ወገኖችን በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ማደራጀት ብሎም ድህነትን በመቅረፍ የኑሮ ደረጃቸውን በማሻሻል ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህም መሠረት ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2009 ለበርካታ ሥራ ፈላጊዎች ለስራ ዕድል ተፈጥሮል፡፡ በተለይም ባሳለፍነው በጀት ዓመት ብቻ ለ5,000 ሥራ ፈላጊዎችየሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ 4183 ወደ ሥራ እንድገቡ ተደርጓል ፡፡ከዚህ ውስጥ ከተሃድሶ ወዲህ ለ1507 ያህል የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ እንድሁም መንግስት ለወጣቶች በለቀቀው ተዘዋዋሪ ፈንድ ከተደራጁ 114 ከማህበራት ውስጥ 595 ወጣቶች ተደራጅተው ከዚህ ውስጥ ለ20 ማህበራት 102 አባላት 3.7 ሚሊዮን ብር ተሰጥቷቸው ስራ ገብተዋል፡፡ በማህበራዊ ዘርፍም በከተማዋ የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በተደረገው ጥረት 1 ሆሰፒታል፤ 2 ጤና ጣቢያዎች፤ 9 የግል መካከለኛ ክሊኒኮችና 4 መድሐኒት ቤቶች ለነዋሪዉ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ በትምህርት መስክም 1 የመንግስት ዩንቨርሲቲ፣ 1 የመምህራን ኮሌጅ፣ 1 ቴክኒክናሙያ ኮሌጅ፣ 1 የመሰናዶ፣ 2 የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ 7 የመንግስት እና 3 የግል አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች አሏት፡፡ የከተማዋ የውሃ ሽፋንም በቅርቡ ከተጠናቀቀው የውሃ ፕሮጀክት ወዲህ በፊት ከነበረው እድገት አሳይቷል፡፡ በፍቼ ከተማ ከመንግሰት መስሪያ ቤቶች በተጨማሪ በከተማዋ የተለያዩ የፌዴራል የልማት ተቋሟት ቅርንጫፎች ይገኙባታል፡፡ እነዚህም የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ቴሌኮምንኬሽን፣ ሁለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አንድ የልማት ባንክ፣ 6 የግል ባንኮች፣ 3 ማይክሮ ፋይናንስ ባንኮች፣ የኦሮሚያ ግብርና ምርምር፣ የኦሮሚያ አፈር ምርምር ማዕከል፣ የመንግስት የዶሮና የከብት እርባታ፣ የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ጥበቃ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የምህንድስና ማሰልጠኛ ማዕከል እንዲሁም የተለያዩ የግል ተቋማት ይገኙባታል፡፡ በኢንቨስትመንት ዘርፍም ከተማዋ በ1996 ዓ.ም ሪፎርም ዉስጥ ከገባች በኋላ በተደረገዉ እንቅስቃሴ የተለያዩ ባለሃብቶች ወደ ከተማዋ መጥተዉ በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ሰፊ የልማት ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ወደ ስራ ገብቶው ለበርካታ ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠር ችለዋል፡፡ በተለይም በሰፋፊ የማነፋክቸርን የኢንቨስትመንት መስክ ላይ ተሰማርተው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል እንደ ምሳሌ የሚጠቀሱ የኦቾሎኒ ቅቤ እና የጂብሰም ማምረቻ ፋብሪካ ይጠቀሳሉ፡፡ የከተማዋን አመታዊ ገቢን በተመለከተ በየዓመቱ የከተማዋን ገቢ ለማሣደግ በተሠራው ስራ መደበኛ እና የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ በ2009 በጀት አመት ብቻ 53 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ተችሏል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የህብረተሰብ ተሳትፎውን በልማት ስራዎች ላይ እንደ ዋና ተግባር በመያዝ እና በማጠናከር ሰፊ የህብረተሰብ ንቅናቄ ተሰርቷል፡፡ የመሠረተ ልማት ዝርጋታን በተመለከተ ባሳለፍነው ዓመት ከተሃድሶ በፊት እና በኋላ በመንግስት በጀት እና በህብረተሰብ ተሳትፎ ከተሰሩት የመሰረተ ልማት ሥራዎች ውስጥ የውስጥ ለውስጥ ጠጠር መንገድ 20.86 ኪ.ሜ፣ ኮብልስቶን 12 ኪ.ሜ፣ የውሃ መሄጃ ቦይ 2.2 ኪ.ሜ እና 0.5 ኪሎ ሜትር የመንገድ ዳር የሸክላ ንጣፍ (ቲራዞ) ተሰርቷል፡፡ በፍቼ ከተማ የህብረተሰብ ተሳትፎን እንደ ማህበረሰብ እሴት በመያዝ ለልማት አስተዋጽኦ እንዲያበረከረቱ በማሳተፍ ረገድ ባለፉት አመታት የተገኙ ውጤቶች አመርቂ ናቸው፡፡ ሌላው ጉዲፈቻ በሀገራችን በስፋት ከሚታወቅበት እና የሌላ ሰውን ልጅ በአደራ ተቀብሎ እንደራስ ልጅ በማሳደግ ነው፡፡ ይህንም ወጣ ባለና በተለየ ዘይቤ እፅዋትን በጉዲፈቻ መልክ ከከተማ አስተዳደሩ ተረክቦና ኃላፊነት ወስዶ በእንክብካቤ የማሳደግ ስራ ይገኝበታል፡፡ ይህን የፈጠራ ሃሳብ ለማፍለቅ የከተማ አስተዳደሩ ያነሳሳው ዋነኛው ጉዳይም ከተማዋን በአረንጓዴ ልማት ለመሸፈንና ህብረተሰቡም የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ለማስቻል ነው፡፡ ውጤታማነቱም በተግባር እየተረጋገጠ ይገኛል፡፡ ሌላው በከተማዋ የህብረተሰብ ተሳትፎን የሚያጠናክሩ አዳዲስ ሐሳቦችን በመተግበር የተገኘው ውጤት እንደ መልካም ተሞክሮ የሚጠቀሰው የአካፋች ወይም አካፍቱኝ ስርአት ሲሆን ይህም በከተማው በሚካሄዱ የህብረተሰብ ተሳትፎ የልማት ስራዎች ውስጥ በአዲስ ፈጠራ የተገኘ ሲሆን ይህ ስርአት ገቢ በማሰባሰብ ረገድ የተዋጣለት ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህም በከተማዋ የሚገኙ ነዋሪዎች በቀበሌዎቻቸው የልማት ተግባራትን በህብረተሰብ ተሳትፎ ለማካሄድ ሲያቅዱ ባዛር በማዘጋጀት የአካባቢውን ታዋቂ ግለሰብ (በከተማው ውስጥ ወይም ከከተማ ውጪ የሚኖር ሊሆን ይችላል) የባዛሩ ዝግጅት ከፋች እንዲሆን በመጋበዝና ከራሱና ከሌሎች አካላት ገቢ እንዲሰበስብ የሚደረግበት ስርአት ነው፡፡ በዚህም ስርአት በአብዛኞቹ ቀበሌዎች በተዘጋጁ ባዛሮች አካፋቾች በርከት ያለ ገንዘብ በማሰባሰብ ለከተማዋ ልማት የበኩላቸውን ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ ለልማት ስራዎች የባዛር ዝግጅት ዋነኛው የገቢ መሰብሰቢያ ዘዴ ሲሆን እያንዳንዱ ነዋሪ በየቀበሌው ባሉ አደረጃጀቶች በኩል ከከተማው አስተዳደር ጋር በመነጋገር የባዛር ዝግጅት በማድረግ ለልማት ስራ የሚውል ከፍተኛ ገቢ የሚሰበሰብበት ነው፡፡ በባዛሩ ላይም አካባቢው እና የቀበሌው ነዋሪዎች፣ የከተማው አስተዳደር እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ በመሆን በዝግጅቱ ላይ የሚቀርቡ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን በጨረታ በመግዛት ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡ የገቢ አሰባሰቡም በህጋዊ ደረሰኝ መሰረት በልማት ቡድኑ ኮሚቴዎች አማካኝነት የሚከናወን ነው፡፡ ከላይ ከተገለፁት በተጨማሪ የከተማዋን ፅዳትና ውበት ለማስጠበቅ ህብረተሰቡን ግንዛቤ በማስጨበጥ ነዋሪው አካባቢውን እንዲያፀዳና በፕሮግራም እንዲመራ የተሰሩ ስራዎች እንዳሉ ሆኖ በደረቅ ቆሻሻ ማንሳት ስራ ላይ የተደራጁ 8 ማህበራትን ከህብረተሰቡ ጋር በማስተሳሰር አስፈላጊው የፅዳት ስራ እንዲሰራ በማድረግ ከፍተኛ ስራ የተሰራ ሲሆን ከተማዋን ፅዱ እና ውብ ከማድረግ አልፎ የስራ ፈጠራው አጋዥ እንዲሆን ተደርጎል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያየዘ የከተማን ፅዳት ለመጠበቅ በተመረጡ ቦታዎች የጋራ የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች ስለሚያስፈልጉ ተዘግተውና አገልግሎት ሳያሰጡ የቆዩ የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች እንዲፀዱና አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ አዳዲስ የህዝብ የጋራ መፀዳጃ ቤቶች በከተማችን ያሉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማስተባበር እንዲሰሩ ተደርጓል፡፡ የአረንጓዴ ልማት ስራውም ከአሁን በፊት በከተማዋ በዘልማድ ከሚተከሉ ባህር ዛፎች ውጪ ከተማዋን አረንጓዴ ለማድረግ ታስቦ የተሰራ ስራ ምንም ያልነበረ ሲሆን ባለፉት አመታት በፕላኑ መሰረት አረንጓዴ ቦታዎችን በመምረጥ እንዲለሙ ተደርገዋል፡፡ በ2009 በጀት አመትም በከተማዋ እየተሰሩ የኮብል ንጣፍ ድንጋይ እና የጠጠር መንገዶች መካከል፣ አረንጓዴ ቦታዎች ላይ በሀገር በቀል ችግኞች ለምተዋል፡፡ ከተማዋን በፍጥነት ወደ አረንጓዴነት ለመቀየር ህብረተሰቡ በጉዲፈቻ መልክ ችግኞችን ወስዶ እንዲንከባከብ እንዲሁም ልማታዊ ባለሀብቶች ከተማ ውስጥ ቆሻሻ ሲጣልባችው የነበሩ ቦታዎችን በማልማት ወደ አረንጓዴ ቦታ ለውጠውታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሰፋፊ አረንጓዴ ቦታዎችን በመለየት 5 ሺህ ካ.ሜ የሚሆን አረንጓዴ ቦታ እና 10 ሺህ ካ.ሜ የሚሆን ቦታ ዘመናዊ የወጣቶች ፓርክ ተደርቷል፡፡ በከተማው ውስጥ ያሉ ጎጦች ውስጥያሉ አረንጓዴ ቦታዎችን ለይቶ ፕላን እንዲሰራላቸውና ለወደፊት ሊለሙ እንዲችሉ በእቅድ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ባለፉት ዓመት የከተማውን ህብረተሰብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ የመሰረተ ልማት ሥራዎች የተከናወኑ መሆናቸው የከተማዋን ዕድገት ወደ ፊት የሚያራምዳት ሲሆን በያዝነው በጀት ዓመትም ይበልጥ የህብረተሰቡን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ዘርፈ ብዙ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ለማከናወን ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል፡፡

በአሰበ እንደሻው

ምንጭ፤ የፍቼ ከተማ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት