News News
Minimize Maximize
« Back

በሀገራችን ተግባራዊ እየሆኑ ላሉ የቤት ፕሮግራሞች ጠቃሚ መረጃዎች

 

 

ቤቶችን ለነዋሪዎች ስለማስተላለፍ

1)  የጋራ መኖሪ ቤቶች ልማት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተገነቡ ጠቅላላ መኖሪያ ቤቶች ብዛት ምን ያህል ነው?

 •  የቤት ልማት መርሃግብር በአዲስ አበባ በ1996 ከተጀመረበት ጀምሮ እስካሁን መጋቢት 2009 ድረስ በ20/80 ፕሮግራም 274,699 ቤቶች እንዲሁም በ40/60 39,229 ቤቶች ግንባታ ተጀምሮ በ20/80 ከተጀመሩት 182,606 እንዲሁም በ40/60 ከተጀመሩት 1,292 የሚሆኑት ተጠናቀው ቀሪዎቹ 130,030 ቤቶች በተለያዩ የግንባታ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል በክልሎች ደግሞ ፕሮግራሙ በተጀመረባቸው ሁለት ዓመታት (በ1999 እና 2000) 68,732 ቤቶች ግንባታ ተጀምሮ 63379 ቤቶች የተጠናቀቁ ሲሆን 5,353 ቤቶች በተለያዩ የግንባታ አፈጻጸም ባሉበት እንዲሸጡ የተወሰኑ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በአዲስ አበባ እና በክልሎች 382,660 ቤቶች ግንባታ ተጀምሮ 247,277 የሚሆኑት የተጠናቀቁ ሲሆን ቀሪዎቹ 173,320 ቤቶች በግንባታ ላይ ያሉ ናቸው፡፡

2)  ከተገነቡ መኖሪያ ቤቶች መካከል ለነዋሪዎች ያልተላለፉ መኖሪያ ቤቶች ብዛትና ምክንያት ምንድነው?

 •  እስካሁን ድረስ በአዲስ አበባ በ20/80 እና 40/60 ከተገነቡት ቤቶች መካከል 173,662 ቤቶች ለተጠቃሚዎች የተላለፉ ሲሆን 10,236 የሚሆኑት ያልተላለፉ ናቸው፡፡ በክልሎችም ከተገነቡ ቤቶች መካከል የተላለፉት/የተሸጡት 61,931 ቤቶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ 1,448 ቤቶች ያልተሸጡ ናቸው፡፡ በጠቅላላው በክልልም ሆነ በአዲስ አበባ 235593 ቤቶች ለተጠቃሚዎች የተላለፉ ሲሆን 11,684 ያህል ቤቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ለተጠቃሚዎች ሳይተላለፉ ቀርተዋል፡፡ በሌላ በኩልም በክልሎች ተጀምረው ግንባታቸው ሳይጠናቀቅ በአሉበት እንዲሸጡ ከተወሰኑት መካከል 1,448 ቤቶች አሁንም ያልተሸጡ ናቸው፡፡ ለዚህም ዋና ዋና ምክንያቶች በአዲስ አበባ ደረጃ ቤቶቹ በተለያዩ ምክንያቶች መጠናቀቅ ባለመቻላቸው፣ ዕጣ የደረሳቸው ተመዝጋቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች ቀርበው ፎርማሊቲውን አሟልተው ቤቶቹን ለመረከብ ባለመቻላቸው፣ ከተገነቡ ቤቶች መካከል ለልማት ተነሺዎችና ለመሳሰሉት ለመጠባበቂያ ተይዘው በመቆየታቸው…ምክንያቶች ሲሆን በክልል ደረጃ ደግሞ ከ2003 ጀምሮ ግንባታቸው ባሉበት እንዲቆምና እንዲሸጡ የተወሰኑ ግንባታዎች/ቤቶች ፍላጎት አለመኖር ነው፡፡

3)  ቤቶች ለነዋሪዎች የሚተላለፉበት መንገዶች ምን ምን ናቸው? ፍትሃዊነታቸው ምን ይመስላል? መኖሪያ ቤት እያላቸው በፕሮግራሙ ተሳትፈው ዕጣ የደረሳቸው ሰዎች ላይ የሚደረግ ቁጥጥር ምን ይመስላል? ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን ምን የተለየ ትኩረት ያገኛሉ?

 •  ቤቶች ለነዋሪዎች የሚተላለፉበት መንገድ ቅድሚያ ለልማት ተነሺዎች መጠባበቂያ በመያዝ ቀሪው ተመዝግበው ለሚጠባበቁት በዕጣ የሚከፋፈል ሲሆን ዕጣውም በቅድሚያ ለሴቶች 30 በመቶ፣ ቀጥሎ ለመንግስት ሰራተኞች 20 በመቶ በሶስተኛ ደረጃ ለአካል ጉዳተኞች 5 በመቶ ከወጣ በኋላ ቀሪው 45 በመቶ ለሁሉም ተመዝጋቢዎች እኩል የሚወዳደሩበት በዕጣ የማስተላለፍ ስርዓት ተዘርግቶ ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል፡፡ ይህም የአፈጻጸም መመሪያ ተዘጋጅቶለት በመፈጸም ላይ ሲሆን ፍትሃዊነቱን ለማረጋገጥ ቀደም ሲል ምንም አይነት ቤትም ሆነ የቤት መስሪያ ቦታ የሌላቸውና በመንግስት ፕሮግራምም ተጠቃሚ ያልሆኑት ነዋሪዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የፍትሃዊ ሀብት ክፍፍል ለማረጋገጥ እየተሰራ ይገኛል፡፡

 •  የቤት ማስተላለፉ የአሰራር ሂደትም በቅድሚያ በቤት ፈላጊዎች ምዝገባ ማስፈጸሚያ መመሪያዎች ላይ የተቀመጡ መስፈርቶችን አሟልቶ የተመዘገቡ መሆንና ለተመዘገቡበት  ቤት በመመሪያው ላይ እንደቤቱ ዓይነት ተሰልቶ በተቀመጠ ወርሃዊ የቁጠባ መጠን መሰረት በቅድሚያ በተከፈተ የባንክ ቁጠባ ሂሳብ ያለማቋረጥ ቆጥቦ ቢያንስ ለቤቱ የተተመነ የቅድሚያ ክፍያ መጠን ማሟላት ይኖርበታል፡፡

 •  ከዚህ በተጨማሪ የቤት ማስተላለፉ ሂደት የሚመራበት የአሰራር መመሪያ የተዘጋጀ ሲሆን ይህን መመሪያ ተከትሎ ከእጣ አወጣጥ እስከ ቁልፍ ርክክብ ድረስ የሚጠበቅበትን መፈጸም ሲሆን ይህም አገልግሎት በአንድ መስኮት አገልግሎት እንዲሰጥ አሰራር ተዘርግቷል፡፡ የማስተላለፉ ሂደት የሚጀምረው መስፈርቱን የሚያሟሉና ለዕጣው ብቁ የሆኑ ተመዝጋቢዎችን በመለየት ለዚሁ ዓላማ በተዘጋጀ ዘመናዊ ሶፍትዌር በታገዘ የዕጣ አወጣጥ ስነስርዓት ሲሆን ስነስርዓቱን በቀጥታ የሚደያ ስርጭት እንዲተላለፍና በርካታ ህዝብና የመገናኛ ብዙሃን በታዛቢነት በተገኙበት በይፋ እንዲካሄድ በማድረግ የሚፈጸም ነው፡፡ በዚህም ሂደት/አሰራር የቤት ማስተላለፉ ይበልጥ ግልጽና ፍትሃዊ እንዲሆን ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፡፡

 •  ቀደም ሲል የራሳቸው ቤት ያላቸው ሆነው ነገር ግን ምዝገባ አካሂደውና ዕጣ የደርሳቸው ተመዝጋቢዎች ቁጥጥርን በተመለከተ በቅድሚያ ቁጥጥሩ የሚጀምረው በምዝገባ ሂደት ተመዝጋቢዎች የተጠቀሰው አካሄድ ህግ ወጥ መሆኑና ህጋዊ እርምጃ የሚያስወስድ መሆኑን አስቀድሞ በምዝገባ ወቅት በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጡና በዚሁ ስሜት የምዝገባ ፎርሙን ሞልተው ፊርማቸውን እንዲያኖሩ በማድረግ ግዴታ በማስገባት ሲሆን በቤት ማስተላለፍ መመሪያና አሰራርም ወቅት ቤት የሌላቸው መሆኑን የሚጣራበትና ግዴታም የሚገቡበት ሁኔታ አለ፡፡

 •  ከዚህ አልፎ ያልተገባ ጥቅም ለማገኘት የሚደረጉ ድርጊቶችን ለመቆጣጠር ከተቀመጡ ህጎች መካከል በተለይ በኢ.ፌዲ.ሪ. የመኖሪያ ቤቶች ልማትና ግብይት አዋጅ ቁጥር../2008 አንቀጽ 30.3 ማንኛውም የቤት ተመዝጋቢ በማንኛውም መንገድ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ከሆነ ለከተማ አስተዳደሩ አሳውቆ ከምዝገባ ስሙ እንዲሰረዝ ማሳወቅ እንዳለበት እና ተመዝጋቢው በራሱ ወይም በትዳር አጋሩ ስም ሆነ ብሎ በዚህ አዋጅ አንቀፅ 25 ስር በተዘረዘረሩት ከአንድ በላይ የቤት ዓይነቶች ተመዝግቦ ከተገኘ የሱም ሆነ የትዳር አጋሩ ስም ሙሉ በሙሉ ከባህር መዝገቡና ከመረጃ ቋቱ እንደሚሰረዝ በግልጽ የተቀመጠው፣ እንዲሁም አንድ ተመዝጋቢ በራሱ ወይም በትዳር አጋሩ ስም በከተማው ውስጥ የመኖሪያ ቤት ወይም የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እያለው ወይም ከዚህ ቀደም የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ ተጠቃሚ ሆኖ ወይም ካሉት የቤት ልማት ፕሮግራሞች ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ የተመዘገበ እንደሆነ ከምዝገባ መሰረዙ ወይም የደረሰውን ቤት በገበያ ዋጋ ከፍሎ የመውሰድ መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ከብር ፲ሺ (አስር ሺህ ብር) እስከ ብር ፶ሺ (ሃምሳ ሺህ ብር) በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚቀጣ የተቀመጠው እና በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 39 ስለጥቆማ ማቅረብ በተቀመጠው ውስጥ ከላይ የተጠቀሱ ድርጊቶችን በፈጸሙ ግለሰቦች ላይ ጥቆማ ቢቀርብ ምርመራ ተደርጎ ጥቆማ የተደረገበት ሰው ባልተገባ አኳኋን ለመጠቀም በመፈለግ ከተመዘበ ወይም ቀደም ሲል ባልተገባ አኳኋን መጠቀሙ ከተረጋገጠ ቤቱ ከደረሰዉ የቤቱን ዋጋ ፲፭ (አስራ አምስት) በመቶ፣ በቤት ፈላጊዎች ምዝገባ የተመዘገበ ከሆነ የቆጠበዉ ገንዘብ 1/3ኛ ተሰልቶ ይቀጣል፡፡ በተለያዩ የመንግስት የቤት ፕሮግራሞች የተጠቀመ መሆኑ ከተረጋገጠ መብቶቹን እንዲያጣ ይደረጋል፡፡ ቤት እያላቸው ምዝገባ ያካሄዱ ግለሰቦችን ለማጣራት የጣት አሻራ ለመውሰድ ታስቦ አስፈላጊ መሣሪያዎችንና የመሳሰሉ ቅድመ ዝግጅቶች ማካሄድ ተጀምሯል፡፡

 •  የአካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን ስለሚደረግላቸው የተለየ ትኩረት በተመለከተ በተለይ የቤት ዕጣ የደረሳቸው አካል ጉዳተኞችና ቤተሰባቸው ተደራሽ የቤት ቅያሪ ማግኘት እንዲችሉ ከፖሊሲና ከህግ አግባብ አንጻር ቀደም ሲል ተዘጋጅቶ በስራ ላይ በዋለው የ40/60 ስትራቴጂ ሰነድና የምዝገባ መመሪያው መሠረት እንዲሁም በቤት ልማትና ግብይት አዋጅ ቁ../2008 አንቀጽ 29.4 መሠረት በእጣ አወጣጥ ወቅት የእንቅስቃሴ አካል ጉዳተኛ የሆነ የቤት ፈላጊ በማንኛውም ፕሮግራም የቤት ፈላጊዎች ምዝገባ መሰፈርት እስካሟላ ድረስ ምርጫው እንደተጠበቀ ሆኖ ተደራሽ በሆነው የህንጻው ወለል ላይ የሚገኝ ቤት የመግዛት የቅድሚያ ቅድሚያ ሊያገኝ እንደሚችል በተደነገገው መሰረት እንዲስተናገድ ተቀምጧል፡፡ በዚሁ መሰረት አካል ጉዳተኞች እና አረጋዊያን የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ ሲደርሳቸው ተደራሽ የሆነ ቤት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማመቻቸት በተጨማሪ በተለይ በአዲስ አበባ ከሚገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች 5 በመቶው የዕጣ አወጣጥ ቅድሚያ ተጠቃሚነት ለአካል ጉዳተኞች እንዲሆን የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ በወሰነው መሰረት ከ11ኛው ዙር ጀምሮ ይህንኑ ተፈጻሚ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

 4)  በዕጣ/ሎተሪ ቤት ለማግኘት የተመዘገቡ ነዋሪዎች ብዛት ምን ያህል ነው?

 •  በአዲስ አበባ በዕጣ/ሎተሪ ቤት ለማግኘት 758,149 የሚሆኑት በ20/80፣ 22,324 ያህሉ በ10/90 እንዲሁም 164,687 የሚሆኑት በ40/60 በድምሩ 945,160 ቤት ፈላጊ ነዋሪዎች የተመዘገቡ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 397,512 ሴቶች ናቸው፡፡

5) ቀሪ ቤቶችን ለነዋሪዎች ገንብቶ ለማስተላለፍ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል? የመገንባትና የማስተላለፍ ሂደቱን በተያዘው ዕቅድ ለማካሄድ ያጋጠሙ ችግሮችና የሚወሰዱ መፍትሄዎች ምንድን ናቸው?

 •  በአሁን ወቅት ከተፈጠረው የፋይናንስ እጥረት አኳያ ቀሪ ቤቶች ገንብቶ ለማስተላለፍ ይህን ያህል ጊዜ ይፈጃል ብሎ መረጃ ለመስጠት ይከብዳል፡፡ ቤቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ግንቦቶ ለማጠናቀቅና ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ ከአጋጠሙ ችግሮች ዋነኞቹ የፋይናንስ እጥረት፣ የግንባታ አቅም እጥረትና የአሰራር ክፍተቶች ናቸው፡፡

6)  ከተመዘገቡ ነዋሪዎች መካከል ምን ያህሉ ቅድሚያ ቁጠባ ይቆጥባሉ? የዚህ ፋይዳው ምንድነው?

 •  ምዝገባው ከተካሄደ ከ2005 መጨረሻ ጀምሮ እስከ የካቲት 2009 ድረስ በ40/60 ፕሮግራም ከተመዘገቡ ቤት ፈላጊዎች መካከል 16,226 ተመዝጋቢዎች (100%) የቆጠቡ፣ 38,791 ተመዝጋቢዎች 40% እና ከዚያ በላይ የቁጠባ ክፍያ ያጠናቀቁ ሲሆን ባጠቃላይ 14,3761 ተመዝጋቢዎች በመቆጠብ ሂደት ላይ (active) ናቸው፡፡ እስካሁን 22,527 ተመዝጋቢዎች ቁጠባቸውን አቋርጠው ከፕሮግራሙ የተሰረዙ ናቸው፡፡

 •  በሌላ በኩል በ20/80 እና 10/90 ፕሮግራምም ከተመዘገቡ 719,177 ቤት ፈላጊዎች መካካል 53,022 የሚሆኑት የቅድመ ክፍያውን ያጠናቀቁ ሲሆን 624,970 የሚሆኑት በቁጠባ ሂደት ላይ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ 125,673 የሚሆኑት ቁጠባቸውን አቋርጠው ከፕሮግራሙ የተሰረዙ ናቸው፡፡

 •  የተቆጠበ ገንዘብን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ባይገኝም በጥቅል በአጠቃላይ በሁሉም ኘሮግራሞች ከብር 25 ቢሊዮን በላይ ለመቆጠብ እንደተቻለ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ይህም የቁጠባው ፋይዳ ሲገመገም የቤት ፈላጊውን ብሎም የከተማ ነዋሪውን ህብረተሰብ የቁጠባ ባህል ማዳበር ከመቻሉ በተጨማሪ የቁጠባ ገንዘቡ በባንኮች በኩል የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ ለማድረግ ያለባቸውን የገንዘብ ፍላጎት በማሟላት ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽዖው የጎላ መሆኑን ነው፡፡

7)  በአቅም ማነስ ምክንያት በሶስቱ ፕሮግራሞች (10/90፣ 20/80 እና 40/60) ተጠቃሚ መሆን ያልቻሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ ምን እየተሰራ ነው? 

 •  በከተማ ቤት አቅርቦት ስትራቴጂ ማዕቀፍ ከተመለከቱት የቤት ልማት አቅርቦት አማራጮች አንዱ ዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማዕከል ያደረገው የ10/90 ፕሮግራም አማራጭ ነው፡፡ ይህን አማራጭ ለመጠቀም የመክፈል አቅም የሌላቸውና በተለይ የከተሞች መልሶ ማልማት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የሚገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለመግዛት አቅም የሌላቸው ዜጎች የከተማ አስተዳደሮች በአነስተኛ የኪራይ ዋጋ በሚያመቻቹት ቤቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት ለሚድረግ ታስቦ እየተሰራ ነው፡፡ 

ምንጭ፡- የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ (ከ/ል/ቤ/ሚ)